የካይሮው ድግስ
ካይሮው ላይ ምን ተደግሶአል?
የካይሮ ድግስ፣ ዕውነት ከሆነ አሰገራሚ ነው። ከዚያ፣ የምንሰማውና የምናነበው ነገሮች ሁሉ ለማመን በአሁኑ ሰዓት አስቸጋሪ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ይህን የሚቀጥለውን ዘገባ አጠናቅሮ ቢጽፈውማ “የሐበሻ ምኞት ነው…” ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ ነበር።
ግን “ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ ” የተባለው የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ፣ ለእኛ ለአንባቢዎቹ ካይሮ ከተማ ተዘዋውሮ ነገሩን፣ ጉዳዩን እዚያ ተከታትሎና አቀነባብሮ ፣ በአባይ ወንዝ ዳር የሚኖሩ ሰዎች የሚደግሱትን ድግስ፣ እኛ እንድናውቀው በአምዱ ላይ ያሰፈረው ታሪክ፣ ግሩምና ድንቅ ነው። መመልከቱም ክፋት የለውም።
ሸዋ ቢሰማ፣ ይደንቀዋል። ጎንደር ቢያውቀው፣ ጎጃም ቢያዳምጠው ይገረማል። የላስታ ጆሮ ወሬው ቢገባ፣ …ትግሬ ቢሰማ፣ ሓማሴን በጨረፍታ ቢነካው ፣ የአፋር፣ የወለጋና የድሬ ልጆች ቢያውቁት፣..እነሱ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ሳይገረሙ አይቀሩም።
“ታማሮድ”፣ አንድ ካይሮ የበቀለ አዲስ እንቅስቃሴ” አመጽ ” ይባላል፣ አለ ብሎ ጋዜጠኛው ድርጅቱን ከአንባቢው ጋር ያስተዋውቃል። ከድርጅቱም ጋር አንዲት ወጣት የ17 አመቱዋን ኮረዳ ተማሪ፣ በሻሽ የተሸፈነች፣ ሃይማኖተኛ፣ ግን ደግሞ ጂንስ ቀሚስ የለበሰች ልጅ አብሮ እሱዋንም ያስተዋውቃል።
እሱዋና ሌሎች እንደእሱዋ ያሉ “የሞስሊም ወንድማማቾች” ተከታዮች- አንዴ እዚያ የፕሬዚዳንት ሙባራክን ውድቀት አብረው ያቀነባበሩ ወጣቶች፣ አሁን ፕሬዚዳንት ሙርሲን በቃን ብለው ለመጣል ቆርጠው እንደተነሱም ጋዜጣው ያትታል።
“…ለጂሃድ (የልጅቱዋ ስም ነው) እሱ ሙርሲ” ከእሱዋ እንዳዳመጠው፣ “…ለአገሪቱ ድሆች ሰውዬው እስከ አሁን ድረስ ምንም አላደረገም። እሱ በትግል ለወደቁት ሰማዕታት ቤተሰቦች ጡረታና ካሣ አልሰጠም። መቼ በሥራ ይተረጎማል ተብሎ በስንት ጉግት ይጠበቅ የነበረው የሞስሊም ወንድማማቾች፣ ያ እነሱ የግብጽ ሕዝብ ትንሣዔ የሚሉት የቆየ ፕሮግራማቸው ግብና ዓላማው፣ አንዱም በሥራ ላይ እስከ አሁን በፕሬዚዳንቱ አልተተረጎመም። እንዲያውም አልተነካም ….አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ አባይን ገድባ በወሃ ጥምና በረሃብ እኛን ለመቅጣት ስትሞክር፣ ዝም ብሎ ይመለከታል።” የሚለውን የልጅቱን የእሮሮ ቃል፣ ጋዜጣው በአምዱ ላይ አሥፍሯል
“… እንዴ! ሙርሲ እኮ እንደ አንቺው የእስላም እሴቶችን የሚቀበል ሰው አይደለም እንዴ?” ሲላት ደግሞ:-
“…ሰውዬው የተቃራኒውን የሚሰራ ሰው ነው። እሱና እላይ የተቀጡት የሞስሊም ወንድማማቾች፣ ደርሰንበታል በድርጅታችንና በሃይማኖቶቻችን ላይ ይቀልዳሉ።”
“እንደገና ልጅቱዋን ላናግራት ብዬ የሚቀጥለውን ሙከራ (ጋዜጠኛው) አደረኩ ይላል። በተቻለው መንገድ ብዙ የእስላም ሃይማኖት ተከታዮች በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተሹመው የተቀመጡ ፣ ይውጡ ትሉ የለም እንዴ? ….እንደዚህ ዓይነቱንስ ሕልም አንቺው እራስሺ፣ ሳላፊስቱዋ ጂሃድ ሙስተፋ፣ እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ታልሚ አልነበረም ወይ? ” ብላት፣ “…ኦ አንተ ደግሞ ትቀልዳለህ! እግዚአብሔር የዚህቺ ዓለም ሰው ሁሉ፣ ኑዋሪዎቹዋ ሁሉ እስላም ይሁን ብሎ ቢፈቅድ ኑሮ፣ እሱ ይህን ከተመኘ ለእሱ ለእግዚአብሔር ምንም እንደማይሳነው አታውቅም እንዴ?… ግን ልንገርህ እሱ አምላክ ይህን አላደረገም። እግዚአብሔር አልፈለገም”…በሚል፣ እሳት የላሰ ሎጂኩዋ፣ እኔን አሳምና እና አስደንግጣ፣ ቀጠል አድርጋ “… ይህን በመረዳትና መሰረት በማድረግ ፣ እኛ ሞስሊሞቹ በምንም ዓይነት የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን፣ አስገድደንና አስጨንቀን፣ እነሱ የእኛን ሃይማኖት እንዲከተሉ፣ ወይም በእኛ ሥር እንዲተዳደሩ ማድረግ የለብንም።” የሚለውን ቃሉዋን ሰነዘረች፣ ጸሐፊው ይላል።
ልጅቱዋ በዚህ አንደበቱዋና አቀራረቡዋ በመጀመሪያ ሃይማኖተኛ እናቱዋን፣ በሁዋላ የተቀሩትን ቤተሰቦቹዋን ጸረ-ሙርሲ እንዲሆኑ አድረጋለች። አሁን አንድም የድጋፍ ድምጽ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ከዚህ ቤተስብ አያገኝም።
“ሁሉም ዘመዶቼንና ጓደኞቼን፣ አቋማቸውን” ኮርታ አስዋ እንዳለቺው “አስቀይሬአቸዋለሁ። የሆነው ይሁን ታዲያ አሁን ሙርሲን ማን ይተካው?” ስላት ፣ … አስባ አስባ የሟቹን የጸጥታ ኃላፊ የ ኦማር ሱሌማንን ስም ጠራችልኝ..” ይላል።
ቀጥሎም ጋዜጠኛው (–ታሪኩ ገና ጀመረ እንጅ አላለቀም–) የዚህ፣ “አመጽ” የሚባለው እንቅስቃሴ ውስጥ፣ ገባ ብሎ ሰዎቹ ማናቸው ? ብሎ ጠይቆ ለመመራመር ፍላጎት ያለው ሰው፣ አንድ የሚያገነዘበው ነገር ቢኖር፣ እሱ ጸሓፊው እንደሚለው እነዚህ ልጆች በአለፈው አመት በተካሄደው አብዮት ፣ በመጨረሻም በደረሱበት ውጤት ያልተደሰቱ፣ ድል የተመቱና በሞስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ጉዞ ፣ በተለይ በፕሬዚዳንቱ በሙርሲ ሥራ ተስፋ የቆረጡ፣ የደከሙ ልጆች ናቸው ” ይለናል።
“በአገሪቱ ውሰጥ ሰላምና ጸጥታ፣ መረጋጋትም በአለመስፈኑም ፣ አንተን አንፈልግም ከሥልጣንህ ውረድ!” ይላል አንድ የተበተነ ወረቀት ላይ የሰፈረ ጥሪ። ቀጥሎም:-
“ሠራዊቱ አሁንም በሕብረተሰቡ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አልያዘም! …ኢኮኖሚው፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አሁንም ተንኮታኩቶ ከወደቀበት ቦታ ለመነሳት አልቻለም!…ግብጽ አሁንም ከአሜሪካን መዳፍ ውስጥ አለወጣችም !” ስለዚህ አንተን ሙርሲን እኛ አንፈልግም፣ ከሥልጣንህ ውረድ ይላል” እሱ ጋዜጠኛው እዚያ የተመለከተው በራሪ ጽሑፍ። ” ለአዲስ ምርጫም በግበጽ የምትቆሙ ፣ ስማችሁን፣ የኢሜል አድራሻችሁን ፣ …የኑሮ ቦታና የመታወቂያ ወረቀት ቁጥር…እዚህ ላይ ጻፉ !” የሚልም ወረቀት ሰውዬው እዚያ ተመልክቶአል።
በየአደባባዩ፣ በየአውቶብስ ማቆሚያዉ፣ በየቡና ቤቱና በየምግብ ቤቱ …ሁሉም ቦታ፣ በመናፈሻ ሜዳዎችና በትላልቅ አውራ ጎዳናዎች ላይ፣ ወዶ ዘማቾቸ በየአለበት ተበትነው ፣ አንዴ በመዚቃ ድግስ ሌላ ጊዜ በሳቅና በደስታ፣ ማንንም ሳይፈሩ ፊርማና ድጋፍ ከኣላፊ አግዳሚው ይሰበስባሉ፣ የፕሬዘዳንቱንም መውረድ ይጠይቃሉ፣ ጋዜጣኛው ወረድ ብሎ ይላል።
የእንቅስቃሴው ማዕከል ከጣሂር አደባባይ እንደማይርቅም ይጠቁምና በቀጥታ ይህ እንቅስቃሴ ከካይሮ አልፎ አሁን በአሌክሳነደሪያ፣ በአሱዋን እና በፋጁም ቢሮውን ከፍቶ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ሰዎች ለማንቀሳቀስ ኣላማ እንደአለው ፣ እንዳንቀሳቀሰም ይመሰክርላቸዋል። በዚህ በያዝነው በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የአሥራ አምስት ሚሊዮን ሰዎችን ፊርማ ሰብስቦ፣ ይህ ድርጅት ሙርሲን ለመጣል ዕቅድ እንዳለው ከመሪዎቹ አዳምጦአል። ከዚያስ ለሚለው ለጋዜጠኛው ጥያቄ አንዱ መልስ ሲሰጥ፣ “…በሩም፣ መንገዱም፣ ለሁለም፣ ለማንኛቸውም እርምጃ ክፍት ነው፣ የሚለውን የፕሬዚዳንት ሙርሲን ቃል፣ ኢትዮጵያን ለማስደነገጥ ሰውዬው የሰነዘሩትን ቃል፣ ፈገግ እያለ መለሰልኝ” ይላል።
ከዚያ እንግዲህ ጋዜጣው ምን ይመጣል? ማን ይሆናል? ዕጣ ዕድሉ ከሙርሲ በሁዋላ ግብጽን ለመምራት ማን እጅ ላይ ይወድቃል? … ለመሆኑ “አመጽ” የሚባለው እንቅስቃሴ ተስፋ አለው ወይ? ወደሚለው ትንተናው ጸሐፊው ይሸጋገራል። እዚያም የሚከተሉት ነገሮች ሰፍረው አንባቢውን አብሮ እንዲያስብበት ይጋብዛል።
የሰላም ኖቤል ሽልማት ተሸላሚው ሞሐመድ ኤል ባራዲ እና የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምር ሙሳ፣ ሁለቱ ፖለቲከኞች ተስፋ እንደሌላቸው ይጠቁማል። በአሥራ አምስት ሚሊዮን ፊርማም ፕሬዚዳንቱ “ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው “እንደማይወርዱም ፣ ሕገ -መንግሥቱም ስለዚህ ነገር ምንም እንደማያነሳ ያትታል። እንዲያውም የሞስሊም ወንድማማቾች የድጋፍ ፊርማ በተራቸው መሰብሰብ እንደጀመሩም ያየውን “ጉድ”ጋዜጠኛው ዘግቦአል።
የአመጽ እንቅስቃሴ አራማጆች ፣ነሽጦአቸው/ ነሽጦት፣ ሙርሲን ለመያዝ ቤተ መንግሥቱን ከቦ፣ ወይም በጥሶ ፣ ዘልቆ ከገባ ፣ የሞሲሊም ወንድማማቾች( ያላቸው ምርጫ ይህ ብቻ ነው) “በአንዱ አካባቢ በግብጽ ግዛት ውሰጥ የእስላም ሪፓብሊክ ለማወጅ ቆርጠው እንደተነሱም” ከእነሱ አዳምጦአል። ለክፉም ለደጉም ተቃዋሚዎቻቸውን ለማስፈራራት ለሙርሲም የድጋፍ ሰልፍ አደባባይ ላይ ወጥተው ለመግለጽ ሃሳብ እንዳአላቸው ደርሶበታል።
የሆነው ቢሆን ፣የመጣው ቢመጣ የፖሊስ ሠራዊቱ የፕሬዚዳንቱን መቀመጫ ቤተ መንግሥት፣ ከእሱም ጋር የሞስሊም ወንድማማቾቸንም ቢሮዎች በአገሪቱ ውስጥ ሁለቱንም “ግቢዎች” ለመጠበቅ ፍላጎትም፣ ኃይልም እቅምም ፖሊስ እንደሌለው ተወዲሁ ገልጾአል። ምክንያቱ፣ ለዚህ ሁሉ የፖሊስ አቅም ማነስ ሳይሆን ፣ እሱ ሳይሆን ጋዜጣው እንደሚለው፣ ምክንያቱ ሌላ ቦታ ነው።
እሱም አንድ በግብጽ ውስጥ ከጥቂት ቀናት ወዲህ የሚናፈሰው ኃይለኛ ወሬ ነው። “…ሙርሲ ከተነካ ሐማስና የሲና በረሃ ላይ በተጠንቀቅ የተሰለፉ የታጠቁ አክራሪ ተዋጊዎች ( ወሬው ይህ ነው) ካይሮ ገብተው የፕሬዚዳንቱን ሕይወትለማዳንና የፖለቲካ ዘመናቸውን ለማስረዘም ድብልቅልቁን ለማውጣት ተዘጋጅተዋል ” የሚለው አስፈሪ ወሬ ፖሊሱንም፣ ከተሜውንም ሰውንም ሁሉ አሁን ግራ አጋብቶታል።
እንግዲህ ካይሮና ግብጽ ሌሎች ከተማዎችም በግርግር ስትተረማመሱ –ይህ ነው የጽሑፉ መልዕክት- ደም በየአለበት ሲፈስ፣ ያኔ! የጦር ሠራዊቱ አገሪቱን ከመበታተን ለማዳን ዘሎ እንደተለመደው በትረ መንግሥቱን ከመጨበጥ አይመለስም ይላል። ግን “የጦር ኃይሉ አመራር በተቃውሞ ሰልፍና በሞስሊም ወንድማማቾች በተበተነ በአንድ አመቱ፣ ይህን ዓይነት እርጃም ዘሎ ገብቶበት ያደርገዋል ማለትና ብሎም መገመት” ጸሐፊው እንዳለው፣ “ትንሽ ያስቸግራል። ” ወጣወረደ ያልታወቀ ድግስ ካይሮ ላይ ተደግሶአል። “በሩም ለሁሉም ነገር እዚያ ክፍት ነው ይባላል። ዕውነት?
ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ ሰኔ 18 2013 (እእአ)